ዩሴፍ አለሙ /የህንጻ ማሃንዲስ/ የመቋሚያ የማህበረሰብ ልማት ድርጅት የበጎ አድራጎት ክፍል ተጠሪ
“ለአስር አመት የማሪዎና ፣የጫት ፣የሲጋራ እና የአልኮል መጠጥ ተጠቃሚና ሱሰኛ ነበርኩ ፡፡ የጀመርኩት በ18 አመቴ ነው፡፡
በዚህም ከእኔ አልፎ ለቤተሰቦቼ ሰላም ማጣት ምክንያት ሆኜ ነበር፡፡ በትምህርቴ እና በስራ ገበታየ ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት ደርሶብኝ ነበር፡፡
ሆኖም በአንድ ወቅት በደረሰብኝ ልዩ ልዩ ጫና ከምጠቀማቸው እፆች ተላቅቄ አዲስ ሕይወት ለመጀመር አሰብኩ ፡፡ ምክንያቱም በነበረኝ ሕይወት ደስተኛ ስላነበር ነው፡፡
በአጋጣሚ ለስራ ወደ ክፍለሃገር ሄጀ ስለነበር የለውጥ ፍላጎቴን ተግባራዊ ለማድረግ ቻልኩ፡፡ያ ወቅት ከእፆች ተጠቃሚነት ነጻ ለመውጣት የሚያስችል ጥሩ መሰረት እንደነበረው እረዳለሁ፡፡
ሌላኛው ጥሩ ገጠመኝ የምለው ደግሞ ከመቋሚያ ማህበረሰብ ልማት ድርጅት ጋር መገናኘት መቻሌን ነው፡፡ ቀድሞ የማላውቃቸውን የአቻ ድጋፍ አገልግሎቶች እና ልዩ ልዩ ለማገገም የሚረዱኝ ስልጠናዎችን በማግኘቴ በዚህ ወቅት ከእፆቹ ብቻ ሳይሆን ለእጾች ተጠቃሚነት ሲገፋፋኝ ከነበሩት ከአደንዛዥ አስተሳሰቦች ራሴን እንድጠብቅና በመልካም ጎኑ እንድበረታታ ምክንያት ሆነውኛል፡፡
በመቋሚያ የማህበረሰብ ልማት ድርጅት የግንዛቤ ፈጠራ ላይ ከመሳትፍ ጀምሮ ልዩ ልዩ ስልጠናዎች ላይ መሳተፊ እንዲሁም ከመሰሎቼ (ከአቻዎቼ) የማገኛቸው ድጋፎች የሕይወቴ ምርጥ ስጦታዎች ናቸው ብየ አምናለሁ፡፡
ለአለፉት 10 አመታት ውስጥ በለውጥ ጎዳና እየተገጓዝኩ በበጎ ፍቃደኝነት በመቋሚያ ውስጥ የበጎ ፍቃደኞች አስተባባሪ በመሆን እያገለገልሁ እገኛለሁ፡፡ ዛሬ በመቋሚያ የአቻ የቡድን ድጋፍ ውይይት ራሴን እያበረታሁ ፤ በስራም ሆነ በጤንነቴ እጅግ ጥሩ ደረጃ ላይ እገኛለሁ ፡፡ “
ዩሴፍ አለሙ /የህንጻ ማሃንዲስ/ የመቋሚያ የማህበረሰብ ልማት ድርጅት የበጎ አድራጎት ክፍል ተጠሪ