አዲስ አበባ

አገር ማለት ሰው ነው፤ ሰው ማለት አንጎል ነው፡ የትውልድ ህልውና እና የተሃድሶ ፍልስፍና

1. መግቢያ፡ አገር እንደ ሰው ስብስብ

አገር በካርታ ላይ የሚሰመር ድንበር ወይም የተከመረ ድንጋይ አይደለችም። አገር ማለት በውስጧ የሚኖሩ ዜጎች ድምር ውጤት ናት። ሰዎች ተስማምተው ስምምነትን (Social Contract) ሲፈጥሩ አገር ትቆማለች፤ አእምሯዊ ስምምነታቸው ሲላላ ደግሞ አገር ትበታተናለች። ስለሆነም፣ የአንድ አገር እድገት የሚለካው በህንፃዎቿ ከፍታ ሳይሆን በዜጎቿ አእምሯዊ ብስለት፣ የእውቀት ጥልቀት እና የፈጠራ ብቃት ላይ ነው።

2. አንጎል፡ የአገር ግንባታ “ጡብ” (The Biological Capital)

የአንድን አገር ህንፃ የምንገነባበት ዋናው ጡብ የዜጎች አንጎል ነው።

  • የአገር ካፒታል፦ የዓለም ባንክ (World Bank) እንደሚያመለክተው፣ የአገራት የኢኮኖሚ እድገት 70% የሚመነጨው ከ”ሰው ኃይል ካፒታል” (Human Capital) ነው። ይህ ካፒታል ደግሞ በአንጎል ብቃት ላይ የተመሰረተ ነው።
  • የሳይንስ እውነታ፦ አንጎል የሰው ልጅ የውሳኔ፣ የፈጠራ እና የሞራል ማዕከል ነው። አንጎል ሲጎዳ አገር የምትገነባበት ጡብ ይፈረከሳል፤ ይህም ወደ ድህነት እና ብስቁልና ይመራል። 130 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ ማለት 130 ሚሊዮን “አንጎል” ማለት ነው። እነዚህን አንጎሎች ከተንከባከብናቸው እና ካሰለጠናቸው ውጤቱ ለአገር ብልፅግና ይሆናል።

3. አደገኛ ዕፅ እና “አደንዛዥ አስተሳሰብ” (The Duel Threat)

የሰው ልጅ ሶፍትዌር (አእምሮ) እና ሃርድዌር (አንጎል) በሁለት ዋና ዋና አደጋዎች ሊወድቁ ይችላሉ፦

  • አደገኛ ዕፅ (Hardware Damage)፦ ሳይኮአክቲቭ ንጥረ ነገሮች አንጎልን ጥገኛ በማድረግ ነፃ ፈቃድን ይገድላሉ። ይህ “የአንጎል በሽታ” የአገርን ጥንካሬ ይሸረሽራል።
  • አደንዛዥ አስተሳሰብ (Software Malfunction)፦ ዕፅ ባይወሰድ እንኳ፣ ሰዎች ለራሳቸውና ለአገራቸው ጎጂ የሆነ አመለካከት ሲይዙ (ተስፋ መቁረጥ፣ ስንፍና፣ ጥገኝነት) ልክ እንደ ዕፅ ሱስ አእምሮን ያደነዝዛሉ።

4. ራዕያችን (Our Vision)

“ከአደገኛ ዕፅ ተጠቃሚነትና ሱሰኝነት እንዲሁም ከአደንዛዥ አስተሳሰብ የፀዳ ባለ ራዕይ ትውልድ በአፍሪካ ላይ ተሰርቶና ተነስቶ ማየት!”

ይህ ራዕይ የሚመነጨው አፍሪካ አንድ ትልቅ አገር ትሆናለች ከሚል ታላቅ ተስፋ ነው። አህጉራዊ ለውጥ የሚመጣው እያንዳንዱ ዜጋ የራሱን የአንጎል ጤና ሲጠብቅ እና በራዕይ ሲነቃ ነው። ትኩረታችን በአፍሪካ ላይ የሆነው፣ አህጉሪቱ ያላትን እምቅ አቅም ለመጠቀም ጤናማና ባለራዕይ አንጎል ያለው ትውልድ ስለሚያስፈልጋት ነው።

5. ተልዕኮአችን (Our Mission)

ራዕያችንን ለማሳካት “መቋሚያ” በአራት ዋና ዋና ምሶሶዎች ላይ ተመስርቶ ይተጋል፦

  1. ማስተማር (Educate)፦ ስለ አንጎል ጤና እና ስለ ሱስ አስከፊነት ግንዛቤ መፍጠር። ሱስ ሊያገረሽ የሚችል የአንጎል በሽታ መሆኑን በማስረዳት፣ ትውልዱ ራሱን ከጥፋት እንዲጠብቅ እውቀት ማስጨበጥ።
  2. ማቅናት (Rectify)፦ በተሳሳተ መንገድ ላይ ያለን ትውልድ ወደ ትክክለኛው የህይወት መስመር መመለስ። አደንዛዥ አስተሳሰቦችን በማረም የዜጎችን ስነ-ልቦናዊ ጥንካሬ መገንባት።
  3. ማደስ/ተሃድሶ (Restore)፦ በሱስ የተጎዳውን አንጎል እና የተሰበረውን ማንነት በተሃድሶ ማከም። ግለሰቡ በራሱ አቅም ቆሞ እንዲሰራ እና እንዲታደስ ድጋፍ (መቋሚያ) መሆን።
  4. ማጥናት (Study)፦ ችግሩን በሳይንሳዊ መንገድ መመርመር። ወቅታዊ መረጃዎችን እና ምርምሮችን መሰረት በማድረግ፣ ለትውልዱ ጄኔቲክስ ጥበቃ የሚሆኑ መፍትሄዎችን ማመንጨት።

6. ማጠቃለያ

“መቋሚያ” ማለት በውድቀት ጊዜ ድጋፍ፣ በመቆም ጊዜ ደግሞ አጋርነት ነው። አገርን ለመገንባት መጀመሪያ ሰውን (አንጎልን) መገንባት ይቀድማል። “መቋሚያ” ይህንን ታላቅ ራዕይ ሰንቆ፣ የአፍሪካን ብርሃን የሚሆኑ ባለራዕይ ዜጎችን ለማፍራት የተነሳ የለውጥ ሃይል ነው።

“አንጎልህን ጠብቅ፤ አገርህን ገንባ!”

Leave a comment